Tuesday, July 25, 2017

ሄሊንግ ሀንድስ ኦፍ ጆይተጋልጠው ህክምና የተደረገላቸው እናቶችን በህይወት ክህሎት፣በስራ ፈጠራና በጤናማ እናትነት ዙሪያ አሰልጥኖ አስመረቀ፡፡



ሄሊንግ ሀንድስ ኦፍ ጆይ የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ለፌስቱላ ተጋልጠው ህክምና የተደረገላቸው  እናቶችን በህይወት ክህሎት፣በስራ ፈጠራና በጤናማ እናትነት ዙሪያ አሰልጥኖ አስመረቀ፡፡ድርጅቱ በዚህ ዘርፍ ከአማራ ሴቶች ማህበር ጋር በአጋርነት ይሰራል፡፡
የህክምና ባለሞያዎች እንደሚገልፁት በሽንት ፊኛና በማሕፀን መካከል የሚፈጠር ቀድሞ ያልነበረ ቀዳዳ ፌስቱላ ይባላል፡፡ ዋና ምክንያቱ ካለእድሜ ጋብቻ፣በወሊድ ወቅት በጤና ተቋም ባለመውለድ በሚያጋጥም የተራዘመ ምጥ አልፎ አልፎም በመውደቅ ፣በህክምና ስህተትና በበርካታ ሌሎች ምክንያቶች  ሴቶች ለዚህ ችግር ሲጋለጡ  በሽታው በሚፈጥረው ሽታ ምክንያት  ከማህበረሰቡ የመገለል፣ ለፍችና አካላቸው በእንቅስቃሴ እጥረት የመተሳሰር ችግሮች ይዳረጋሉ፡፡
 ይህን ለውስብስብ የጤና እክሎች የሚዳርግ በሽታ ህክምና በ 1959 በዶክተር ካትሪን ሀምሊን ተጀምሮ የበርካታ ሴቶችን ህይወት ከአካላዊና ከስነ-ልቦና ቀውስ መታደግ ከተጀመረ 50 አመታት ቢቆጠሩም ከህክምናው ባለፈ ሴቶች ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ ምን ይገጥማቸዋል፣ምንስ ይሰራሉ፣የስነ-ልቦና ጉዳታቸው እንዴት ይጠገናል የሚሉት ጥያቄዎች መልስ አልባ ስለነበሩ ሴቶች በሚደረግላቸው ህክምና ከአካላዊ ህመማቸው ቢፈወሱም አእምሯዊ ቁስላቸው ሳይፈወስ ስለሚቀር ወደ ቀያቸው ለመሄድ መቸገርና በከተማ የመቅረት፣የችግራቸው መንስኤ በማድረግ ወንድ የመጥላት፣ትዳራቸውን እንደፈቱ በፍርሃት ከጋብቻ መታቀብ፣ዳግም ላለመውለድ በመፍራት ፍች መጠየቅ የመሳሰሉ ውስብስብ  ችግሮች ይዳረጉ ስለነበር ይህን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ስራ በመስራት ላይ የሚገኘው ሄሊንግ ሀንድስ ኦፍ ጆይ ሴቶችን ከህክምና በኋላ በመረከብ ህይወታቸውን በመሰረታዊነት ሊቀይሩባቸው የሚችሉ ስልጠናዎችን ከመስጠት ባለፈ በአማራ ሴቶች ማህበር አማካኝነት የሚፈፀም ከወለድ ነፃ የተዘዋዋሪ ብድር ገንዘብ በመልቀቅ ሴቶች የተሰጣቸውን ስልጠና መሰረት አድርገው ሰርተው እንዲለወጡና ቤተሰባቸውን በማስተዳደር አርአያ እንዲሆኑ በተለይም እነዚህ እናቶች በጤናማ እናትነት አምባሳደር በመሆን እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ በማስተማር እነሱን የገጠማቸው ችግር በሌሎች እንዳይደርስ ከማድረግ ባለፈ ለፌስቱላ ተጋልጠው በቤታቸው ተደብቀው የተቀመጡ ሴቶችን ወደ ህክምና ተቋሙ በማምጣት ህክምና እንዲያገኙ የሚያደርጉ የተቋሙ ሰንሰለቶች በማድረግ በየጊዜው እያስመረቀ ወደ ቀያቸው ይመልሳል፡፡
በዚህም በለጋ እድሜያቸው ሳቃቸው የጨለመና ከሰው ተራ ወጥተው ተስፋቸው በጠዋት የተነነ የመሰላቸው ሴቶችን የጠዋት ሳቃቸውን የመለሰ፣ወልዶ የመሳም ተስፋቸው በምን ሰርቼ ሳይጨነግፍ ሰርተው ከሰው ተራ የተሰለፉ በርካታ እናቶችን ለውጤት እያበቃ ይገኛል፡፡

No comments:

Post a Comment